Thursday, June 13, 2013

መነገር ያለበት ቁጥር 6 "ትግሉ ኑረምበርግ ደርሷል" በልጅግ ዓሊ

መነገር ያለበት ቁጥር 6
<<ትግሉ ኑረምበርግ ደርሷል>> <<ትግሉ ኑረምበርግ ደርሷል>>
በልጅግ ዓሊ
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በሜይ 29/1993 በምዕራብ ጀርመን በሚገኝ ዞሊንግን (Solingen) በሚባል
ከተማ አራት የናዚ ተከታዮች ቱርኮች ይኖሩበት የነበረውን ቤት አቃጥለው እንቅልፍ ላይ የነበሩትን 5 ሰዎችን
ገድለው 15 አቁስለዋል። የዚህ አሰቃቂ ድርጊት ሃያ አመት መታሰቢያ ዝግጅት በቅርብ በጀርመን ውስጥ
ተከታትየው ነበር። ይህ ድርጊት በዓለም ላይ ባስነሳው ተቃውሞና የጀርመን የስደተኛ ሕግ በመቀየሩ ምክንያት
የስደተኛው ቁጥር በመቀነሱ በውጭ ሰዎች ላይ ይደርስ የነበረው አደጋ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ባንልም
ቀንሷል። ዛሬ እነዚህ ይህንን ወንጀል የፈጸሙ 4 ወጣቶች ከ10 ዓመት እስር በኋላ ነጻ ወጥተዋል። የተገደሉት
እናትና አያት የሆኑት ባልቴት ባደረጉት ንግግር በሰላም አብሮ መኖር ጥቅሙን ካስረዱ በኋላ <<እኛም
እናንተም እዚሁ ነን>> በሚል ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
ናዚዎቹ የውጭን ዜጋ ማጥቃት የጀመሩት ከዚህ ወንጀል ቀደም ብሎ ነው። ከ1989 ጀምሮ በጀርመን የናዚ
ተከታዮች የውጭ ሃገር ዜጎችን ከመደብደብ አልፈው ቤታቸውን እስከማቃጠልና እስከመግደል የተደረሰበት
ወቅት ነበር። በመስከረም ወር 1991 ሆየርስቭረዳ(Hoyerswerda)፣ በነሃሴ 1992 ሮስቶክ( Rostock)፣ በህዳር
1991 ሁለት ሴቶችና አንድ ወጣት ሴት የቱርክ ዜጎች ሜልን (Mölln) ከተማ ውስጥ በእሳት አቃጥለው
ገድለዋል። የቆዳችን ቀለም ጥቁር በሆነው ላይ የሚደርስብን በደል እጥፍ ድርብ ነበር። በተለይ በጀርመን
ምስራቁ ክፍል ማለትም የድሮው ኮምኒስት ሃገር ዘረኝነቱ የከፋ ሲሆን እዚያ አካባቢ የሚኖሩ አፍሪካውያንን
የዘርኝነቱን ዋና በትር ቀማሾች ነበሩ።
እንዲህም ሆኖ በ1991 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የጀርመን የስደተኛ ጣቢያዎች በስደተኞች ታጭቀው
ነበር። ከእነዚህ ስደተኞች ውስጥ አንዱ ነበርኩ። ወቅቱ በስደተኛው መንደር ከተለያየ ቦታ በሚሰማው
የናዚዎች እንቅስቃሴ ምክንያት ጭንቀት የሞላው ነበር። ይህ በስደተኛው መካካል የተፈጠረው ጭንቀት
ሥራና የገቢ ምንጭ የፈጠረላቸው ግለሰቦችም ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ በጣም የሚያስደንቀኝ ስደተኞች
የነበረባቸውን ጭንቀት በመጠቀም ሐይማኖታቸውን ለማስፋፋት የሚጥሩና በየስደት ጣቢያው ይጎርፉ የነበሩ
የተለያዩ ሐይማኖት ተከታዮች ናቸው። የጴስጤቆንጤ፣ የጀሆቫ፣ የአዲሱ አፖስትሊክ ቤተክርስትያን . . .
ሌሎችም። ለሐይማኖተኞቹ አዲስ ተከታይ ለማበጀት ይህ በስደተኛው መንደር የተፈጠረው ጭንቀት ምቹ
ነበር። ሙሉ ቀን እየተመላለሱ በመስበክ ስደተኛውን የሐይማኖታቸው ተከታይ እንዲሆን ይጥሩ ነበር።
ስደተኛውም በዚህ ጭንቅ ወቅት ከእግዜር ላለማጣላትም ይሁን ከሰባኪ ጀርመኖች ጥቅምን በመሻት
ሐይማኖተኞቹን መከተል ጀምሮ ነበር። ሐይማኖታቸውን የቀየሩም ትንሽ አይደሉም። በነገራችን ላይ በዚያ
ጭንቀት ወቅት ሐይማኖቱን ተቀብለው የተቀየሩና እስከ አሁን የጠኑ ስደተኞች ቢኖሩም ብዙሃኑ ግን ጭንቀቱ
ሲያልፍ ወደ ቀደምት ሐይማኖታቸው ተመልሰዋል።
ከስደተኛው ጣቢያ ፊት ለፊት አንድ የጀርመኖች ቡና ቤት ነበር። ሙሉ ቀን ሲጃራና ዕጽ እያጨሱ፣
መጠጣቸውን እየጠጡ ሲራበሹ የሚውሉ ጀርመኖች የበዙበት። ቢሆንም ከላይ የጠቀስኳቸው ሐይማኖተኞች
ድፍረቱን አግኝተው ጀርመኖቹን ከዚህ የኃጥያት ድርጊት እንዲቆጠቡ ለመምከርም ሆነ ወደ
ሐይማኖታቸውም ለማምጣት አይጥሩም ነበር። ጀርመኖቹ የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ ስላልነበር
ሐይማኖተኞቹን እንደማይሰሙ የታወቀ ነው።
በእነዚያ የጭንቀት ቀናት ውስጥ በአንዱ የጴንጤውና የጆሆቫው ተከታይ የነበሩትን አገናኝተን ያከራከርናቸው
ይታወሰኛል። ጥያቄው መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ነበር። ማንም ግለሰብ በልሳን መናገር ይችላል ብሎ
በሚያምነው ጴንጤና በልሳን መናገር ይቻላል ብሎ በማያምነው ጆሆቫ መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን
በትክክል ልንረዳው እስክንችል ድረስ ክርክሩ ጦፎ ነበር። ያም ሆነ የሁለቱ ሐይማኖቶች ተከታዮች
ተከራክረው በሰላም ተለያይተዋል።
ወደ ተነሳሁበት ዓላማ ልመለስና ባለፈው ሳምንት በጀርመን የናዚዎች ግድያን በሚመለከት በተዘጋጀ ዝግጅት
ላይ ተሳትፌ ነበር። በዚሁ አጋጣሚም የማያቋርጠው ዝናብ በአካባቢው ከሚኖሩ ዜጎቻችን ጋር ቁጭ ብለን
ለመወያየት ፋታ ሰጥቶን ስለ ነበር ሰለ ሃገር ጉዳይ ተነስቶ በተለይም በጀርመን የኢትዮጵያውንያንን እንቅስቃሴ
ተመልክተነው ነበር። በዚህ አጋጣሚ የዝናቡ ብዛት ከፈጠረው የውሃ መጥለቅለቅ ዜጎቻችንን አንድ አምላክ
በሰላም ይጠብቅል ዘንድ ጸሎታችን ነው። 2
ከመካከላችን አንዱ እንደ ቀልድ <<<<<<<<ትግሉ ኑረምበርግ ደርሷል ትግሉ ኑረምበርግ ደርሷል ትግሉ ኑረምበርግ ደርሷል>>>>>>>> አለን። ሁላችንም ቀልዱ ስለገባን ስቀን
የጀርመንን የኢትዮጵያውያንን ጸረ ወያኔ ትግል አማነው። በአሁኑ ወቅት አዲስ የሚመጡ ስደተኛ ዜጎቻችን
ጊዜያዊ መጠለያ የሚሰጣቸው ኑረንበርግ በሚባለው ከተማ አካባቢ ሲሆን ከመጠለያው ቢወጡም
የሚመደቡትን እዛው ክፍለሃገር ውስጥ ነው። እነዚህ ስደተኞች ገና ጉዳያቸው ያልተፈጸመ ስለሆነ የፖለቲካ
ጥያቄያቸውን ለማስፈጸም የጀርመን ሕግ ስለሚያስገድድ የፖለቲካ ድርጅቶችን ድጋፍ እንደ ማስረጃ ማቅረብ
ይኖርባቸዋል። በዚህ ምክንያት ጭንቀት ስላለባቸው (ያኔ በኛ ዘመን እንደነበሩት ሐይማኖተኞቹ) ይህ
ጭንቀት አመቺ ሁኔታ የፈጠረላቸው <<የፖለቲካ ድርጅት>> ነን የሚሉ በዚያ አካባቢ ያንዣብባሉ። በሌላው
የጀርመን ክፍለ ሃገሮች የተፋዘዘው ትግል እነዚህ አዲስ የመጡትን ስደተኞች ኮቴ ተከትሎ ኑረምበርግ ላይ
በማበቡ ነበር <<ትግሉ ኑረምበርግ ላይ ደርሷል>> የሚለው ንግግር ያሳቀን።
ከድሮው የተለወጠና ሁላችንም ያሳዘነ ጉዳይ ቢኖር ድሮ (ድሮ ልበለውና) የነበረው የፖለቲካ ድርጅት (
የመድህን፣ የኢሕአፓ፣ የመላ አማራ ወዘተ)አባልነት ቀርቶ በአሁኑ ወቅት በግለሰብ ስም የእከሌ ድርጅት፣
የእከሌ ፓርቲ በመባል ግለሰቦች ያቋቋሙት የይስሙላ የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ምልመላ የተጧጧፈ መሆኑ
ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከአባልነት የሚገኘውን የመዋጮ ጥቅም ግለሰቦች ይከፋፈሉታል የሚባለው ሃሜት
መጉላቱ ደግሞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። አባል ሁኜ ውስጡን ስለማላውቅ እርግጡን መጻፍ ቢቸግረኝም
ለድጋፍ ወረቀት፣ ለአባልነት፣ መጽሔት ላይ ጽሁፋቸው እንዲወጣ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ሲመጡ ለመምጣታቸው
ማረጋገጫ ለመስጠት፣ በአማርኛ የተጻፈውን በጀርመንኛ ለመተርጎም በሚል ስም የሚከፈለው. . . ሌላም
ሌላም ከከፈሉት ስለሰማሁት ብዙ መሆኑን መገንዘብ ችያለሁ። (ይህንን ወደ ፊት በሰፊው የምመለስበት
ስለሆነ እዚህ ላይ ልግታው።)
እነዚህ ስደተኞች እንደ ሐይማኖቱ ችግራቸው ሲቃለል የሃገራቸውን ጉዳይ እርግፍ አርገው ቢተውት ምንም
ልንታዘባቸው አይገባም። ለነገሩ እነዚህ የግለሰብ ንብረት የሆኑት <<የፖለቲካ ድርጅቶችም>> ቢሆኑ እነርሱን
ትተው ወደ አዲስ ወደሚመጡትና በቀላሉ የገንዘብ አስተዋጽዖ ወደሚያደርጉት ትኩረት ስለሚያደርጉ ችግር
የለም። ያም ሆኖ የወያኔ እንግልት ያማረራቸው ቆርጠው ከትግሉ ጋር የሚቀጥሉም ብዙ ናቸው። እንደ
ሐይማኖተኞቹ ወደ ጀርመኖቹ መሄድ እንደቸገራቸው <<ፖለቲከኞቹም>> የመኖሪያ ፈቃዳቸው ጉዳይ ወደ
ተፈጸመላቸው መሄድ እንደደበራቸው መቅረት የለበትም ማለት ይቻል ይሆናል። ግን ጉዳዩ ሌላ ነው። መባነን
የሚባል ጉዳይ አለ።
ዛሬ የመኖሪያ ፈቃድ ችግራቸው የተቃለለላቸው ብዙዎቹ በጀርመን ያሉ ስደተኞች የድርጅት አባል ሆነው
የረዱ ከዛም አልፈው ሃገራቸውን ያዳኑ መስሏቸው ብዙ መስዋዕትነት ያደረጉ ይገኙባቸዋል። ከሕዝብ ገንዘብ
ሰብስበው ለድርጅቶቻቸው ልከዋል። ከዚህ በፊት ገንዘብ የጠየቋቸው ሰዎች ትግሉ የት ደረሰ? ብለው አሁን
ቢጠይቋቸው << ትግሉ ኑረምበርግ ገባ! እንኳን ደስ አላችሁ! በአሁኑ ወቅት ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ኑረምበርግ
ላይ ጠርተናል! ተገኙና ገንዘብ አዋጡልን ! ሃገር አድን ዘመቻ ላይ ነንና ! >> ቢሏቸው ምን ያህል እንደሚስቁ
መገመት ይቻላል። ከ22 ዓመት ፀረ ወያኔ ትግል በኋላ ኑረምበርግ ላይ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሳባ? የባነነ ባኗል።
ያልባነነ ከእነዚህ ታላላቅ ስብሰባዎች ምን እንደሚጠብቅ መገመት ያዳግታል።
የሰበሰቡትን ገንዘብ በመጠቀም መሪዎቹ ሙሉ ሰዓታቸውን በትግል ላይ ያሳልፉ ይሆናል ብለው ሲያስቡ
ያገኙት መልስ ሌላ ነው። መሪዎቹ ትግሉን ሃገር ውስጥ ያገባሉ፣ እነሱም ታጋይ ይሆናሉ ብለው ሲጠብቁ
የፈጠሩት ታጋይ ሳይሆን የራሱን ድርጅት በወያኔያዊ መንገድ የሚከፋፍል፣ በተሰበሰበው ገንዘብ የሚንደላቀቅ
ቅምጥልን ነው። ለዚህ እማኝ የሚጠይቅበት ካለ የሃያ ሁለት ዓመት ትግሉን ወደ ኋላ ዞሮ ማየት ነው። ከዛም
ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ይባንናል።
ያም ሆነ ይህ ይህንን አስከፊ አረመናዊ የወያኔ አገዛዝ ለመጣል ትግሉ መቀጠል አለበት። ግን እንደተለመደው
በውጭ ከከተማ ከተማ እየተዞረ <<ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ>> መጥራት ሳይሆን በሃገር ውስጥ ስሞኑን
እንደተጀመረው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍን በመጥራት፣ ታላቅ የስራ ማቆም አድማን በማስተባበር፣ ወዘተ ወያኔን
መጋፈጥ ነው የሚያስፈልገው።
እኔ በበኩሌ ለእነዚህ 22 ዓመት መፍትሄ ላልሰጡ <<ታላላቅ ሕዝባዊ ስብሰባዎች>> ጥሪታችንን ማባከን
አሁንም በሕልም ቅቤ እንደመጠጣት ነው። በየአውሮፓውና ሰሜን አሜሪካ ጸጉር እየሰነጠቁ፣ አማርኛቸውን
እያሳመሩ ቅራኔን የሚገምዱ <<ታጋዮችን>> በውጭ የሚገኘው ዜጋ <<ሂዱና ታገሉ>> ሌላቸው ይገባል።
22 ዓመት በኋላ ማድረግ ያለበን ትንሽም ትሁን ትልቅ በሃገር ቤት ውስጥ የሚደረገውን ትግል መርዳት ነው።
የሚረዳ አይጠፋም። ከረዳናቸውም ብዙ የሚሰሩ ይኖራሉ። በቅርብ የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፉም ይሁን
የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን የጀመሩትን እንቅስቃሴ ብንረዳ፣ ሌሎችም በዚሁ መንገድ ትግሉን
ሊያጧጡፉ ይችላሉ። ድልም ሊቀርብ ይችላል። ከዚህ በተረፈ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ <<ታላላቅ>> 3
ስብሰባዎች በመጥራት መኖራቸው እንዳይዘነጋ የሚጥሩትን ለራሳቸው ራሳቸው ያስባሉና ትኩረት መስጠት
አያስፈልግም። የሃገር ቤቱን ትግል ለመርዳት ከሚደረጉ ስብሰባዎች ሌላ በትልልቅ ከተሞች የሚደረጉ የራስ
ማስተዋወቂያና የአባላት መሸንገያ ስብሰባዎች ማክተም አለባቸው።
ይህ ጽሁፍ የብዙ <<ቆራጥ>> የራስ ጥቅም ታጋዮችን ስለሚነካ በተደለመደው ሁኔታ ስም እየቀያየሩ ዘለፋን
የሚጽፉ በየድረ ገጹ አይጠፉም። ሙሉ ጊዜያቸውን በሕዝብ ገንዘብ እየተንደላቀቁ እንዲታገሉ የተፈቀደላቸው
ስለሆነ ጥቅማቸው ለማስጠበቅ ቢዛለፉ እኔ በቅድሚያ ይቅር ስላልኳቸው እናንተም ይቅር በሏቸው። በ22
ዓመት በኋላ መባነናችን ጥፋት መስሏቸው ይሆናልና። ዋናው ቁም ነገር ግን ይሂዱና ወያኔን ይታገሉ።
ስለ ራሱ የሚያስብ ራሱ ያስብ !
ስለዚያች ሃገር የሚያስብ ግን በሰላም ይክረም! ።
በልጅግ ዓሊ
Beljig.ali@gmail.com
ግንቦት 30/2005 - ሎንዶን