Wednesday, January 9, 2013

መምህሩ እንደ እረኛ ተማሪው እንደ መንጋ! -ታደለ መኩሪያ tadele@shaw.ca

መምህሩ እንደ እረኛ ተማሪው እንደ መንጋ!
እንዲህ ያለ ዘመን ፣ዘመነ ጋንድያ፤
ሰው እንዴት ይሆናል፣ ከርሞ እንዳ ጥጃ፤
በሃገራችን  ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ  ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ይገለፃል። ይህንንም ለማስቆም በትምህርቱ
ዓመት  መጀመሪያ ላይ የተመዘገቡትን ተማሪዎች ቁጥር መምህራን ተረክበው በዓመቱ መጨረሻ  ማስረከብ እንዳለባቸው
ለመፍትሔነት  ቀርቧል። መምህራንም የደረጃ  እድገት፣
የደመወዝ ጭማሪ  ለማግኘት የተረከቧቸውን ተማሪዎች ቁጥር
ሳይቀነሱ ማስረከብ እንደሆነ  ተገልጿል።
ይህን ዓይነት ቁጥጥር በሰሜን ኮሪያ ‘labor Camp’ እሥር
ቤቶች መሰል ጣቢያዎች በተቋቋሙ ትምሀርት ቤቶች
የሚሠራበት  መመሪያ ነው። ይህ ዓይነት መመሪያ
በማስተማርና በመማር ሥራው ላይ አደጋ አለው። መምህራን
ከቀለም አባትነታቸው ይልቅ ያለተማሪው ፍላጎት
ተቆጣጣሪዎች ያደርጋቸዋል።በሰባዐዊ መብት ገፋፊት
ያስፈርጃቸዋል።ተማሪዎችም  ቢሆኑ መብታቸውን የገፈፈውን
መምህር ለብቀላ  ለወያኔ እንዲሰልሉት መንገድ ይከፍታል።
ይህ ድርጊት በሰሜን ኮሪያ እየተሠራበት ነው። ለግንዛቤ ያህል በአንድ ወቅት የሰባዐዊ መብት ተከራካሪ  ተማኝ በየነ መለስ
ዜናዊ ከመሞቱ ሰምንት ወር ቀደም ብሎ እንዲህ ብሎ ነበር፤  ‘ጠቅላይ ሚስትር መለስ ዜናዊ  ቢሞት፣ እንደሰሜን ኮሪያን
ሕዝብ ለኬሚን ሱንግ አስገድደው  እንዳስለቀሱት፤ መለስ ቢሞት  ወያኔ መላውን  የኢትየጵያን ሕዝብ ያስለቅሱታል’  ያለው
ትንቢተ ደረሰ። ይህ አሁን ወያኔ ትምህርትን አስመልክቶ እያደራ ያለው ድር  የዘርና የጎሣው ክፍፍል ሌላው አካል ነው።
አንዳንድ በውጭ የሚኖሩ በጎ አሳቢ ‘wishful thinkers’  መሰል ምሁራን እኛ ስለፖለቲካው አያገባንም፣ ግን ስለትምህርት
እድገት ምርምር አድርገን የትምህርቱ ሥራ ግቡን እንዲመታ አስተዋጾ እናደርጋለን ሲሉ ይደመጣሉ። ‘ለሥጋው ጾመኛ ነኝ፣
ከመረቁ ሰጡኝ’ አባባል ይመስላል። ‘እንኳን አቺን የዝንብ ጠንጋራ አናውቃለን’ ይላል የሃገሬ ስው! የወያኔ ፖለቲካ
ያልገባበትና ሊቆጣጠረው የማይፈልገው መሥሪያ ቤት ወይም የሥራ መስክ የቱ ነው?  ሕዝብን እርስ በርሱ  ማናከሱ አንሶት
በትምህርቱ  መስክ አዲስ ደባ አቅዷል። መምሀሩም ተማሪውም  በአንድነት እንቢኝ ማለት ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ ቀደም የትምህርቱን ሥራ አስመልክቶ  በድህረ ገጾች ሁለት መጣጣፎች አድርጌ ነበር።’ በድንቁርና ላይ ወሮሸባ እንበል’
እና ‘መምህሩም ያስተምር ተማሪውም ይማር’ የሚሉ ነበሩ። ጠቅላላ ይዘታቸው የትምሀርቱን ሥራ አስመልክቶ በባለቤትነት
ሕበረተሰቡ መምከር እንዳለበት ጦቁሜለሁ። የትምህርቱ ሥራና የፖለቲካው ሥራ ለየቅል መሆናቸውን ለማሳየት ሞክሬለሁ፤
ዜጎች የሚጎዳቸውን ከሚጠቅማቸው ለይተው የሕይወታቸው መመሪያ ለመንደፍ ትምህርት አማራጭ የሌለው መሣሪያ
እንደሆነም ገልጫለሁ። ልጆቻቸው ተኮትኩተው የሚያድጉበትን ሥረዓተ ትምህርት ለመቅረጽ ሐሣብን በነፃነት መግለጽ
ቅድሚያ  የሌለው ቅድሚያ መሆኑን ጠቁሜአለሁ። የዓለም ሕብረተሰብም ይህንን አውቆ  የማወቅና የማሳወቅ መብት ፍጹም
ያልተገደበ ነው። በእኛ ሃገር የሕብረተሰቡ አካል የሆኑት መምህራንና ተማሪዎች ሐሣባቸውን ሲገልጹ ሲታሰሩና ሲገደሉ ነው
ያየነው።የወያኔ መንግሥት የትምህርት ሥራው ማሽቆልቆሉንና የተማሪው ለትምሀርት ያለው ፍላጎት እየቀነሰ መምጣቱን አሌ
የሚለው አይደለም። ምክንያቱንም አያውቀውም ማለት አይቻልም። ለተማሪው የመማር ፍላጎት ማጣት የትምህርት ሥራው
ውጤት ማሽቆልቆል መምህራንና ተማሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ ቂልነት ነው። ሐቁን  ግን ሰው ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ነው።
ለተማሪው ትምሀርት ማቋረጥ ሆነ ለትምህርቱ ማሽቆልቆል ተጠያቂው በመሣሪያና በስለላ ኃይሉ ጉልበቱን አፈርጥም
በማያውቀው የትምህርቱ ሥራ ላይ የሚቦራጨቀው ወያኔ ብቻ ነው።
ስለመገናኛ ብዙሃን ለትምሀርቱ ሥራ የቱን ያህል አስተዋጾ እንደላቸው ባለፈው ጹሑፌ ጦቅሜ ነበር። ከሃገር ቤት በኢ ሜ ል
የደረሱኝ መልክቶች ‘አንተ የደላህ ነህ ሙቅ ታኝካለህ’ መሰል ነበሩ። ሌላው ቀርቶ እንደቀድሞ ዓመታት ተማሪዎቹን
የሚያቃቁ ተግባሮች ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ አይተዩም፤ ሌላው ቀርቶ  በትምህርት ቤቶች መጫወቻ ኳስ የለም ፣
ተማሪውም ሆነ አስተማሪው ኳስ የሚጫወቱባቸውን ትጥቅ ማሟላት አይችሉም፤ ተማሪ በጠኔ የሚወድቅበተ ሃገር እኮ ነው
ያለን እያሉ   ኢ ሜ ል አድርገወልኛል።መጫወቻ ሜዳዎች ቁሻሻ ለብሰዋል፣ የድራማ፣ የክርክር፡ የሰፓርት ውድድር  የሳይንስ
፣ የዛፍ ተከላ፣ የወላጅ ቀን፣ሁሉም የሉም። ዩኒቭርሲቲ ተከፈተ እንጂ አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ተገነባ ሲባል የሰማ አለ?
የቀድሞቹስ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  የተማሪዎች መቀመጫ አላቸው። አንደንድ ትምህርት ቤቶች ተንደው
ሕፃናት ዳስ በመሰሉ ቤቶች ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ አሉ፤ በዙዎቹ አቋርጠው ይሄዳሉ። በኦሮሚያ ኦቢዲዎ
አስተዳደር ስንት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገነቡ? የነበሩት ፈርሰው እንደሆን እንጂ አንድም አልተሠራም።
ሕብረተሰቦች በቋንቋቸው እንዲማሩ ተደርገዋል ተብሏል። በቂ መጽሐፍቶች በተባለው ቋንቋ ጥራታቸውን  ጠብቀው
ቀርበዋል? የሕብረተሰቡን ፍላጎትስ የሚያጸባርቁ ናቸው? ይህን ሆድ ይፍጀው። ቋንቋችን ተከበረ ባሕላችን ታወቀ የሚሉት
አፍቃሪ ወያኔዎች፤ ሐቁ ልጆቻቸውን ትልልቅ ከተማዎች ልከው የሚያስተምሩ ናቸው። ያውም በሚያወግዙት ቋንቋ፤
የሚወክሉትን ሕዝብ ግን ባልተሟላ የትምህርት መሣሪያና  ባልተጠና  ሥረዓት ትምህርት ያደነቁሩታል። ተማሪው
ትምህርቱን ቢያቋርጥ እንዴት ይፈረድበታል? መምህሩስ እንዴት ማስቆም ይቻለዋል?
ዛሬ ተማሪን እንደመንጋ  መምህሩንም እንደ እረኛ በሆነበት አካባቢ የመማርና የማስተማር ጣምና ለዛ የሌለው መራራ ነው።
የዕውቀት ገበታ ሊሆን አይችልም።
ሃገርንና ራሱን የፈጠረ ሕዝብ የሚበጀውን ከራሱ በላይ የሚያውቅለት የለም እና ማንነቱ ከመጥፋቱ በፊት ከዕንቅልፉ መነሣት
አለበት። መምህሩንና ተማሪውን ተጠያቂ ማድረግ ከሐላፊነት ከመሸሽ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም።    
ዓምላክ ኢትዮጵያን ይታደጋት!
ታደለ መኩሪያ
tadele@shaw.ca

No comments:

Post a Comment