Thursday, March 26, 2015

በውኑ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በኢትዮጵያ በ2007 ይታሰባል ወይ? Ezra Feleke ዕዝራ ፈለቀ

Ezra Feleke   ዕዝራ ፈለቀ


 በውኑ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ይታሰባል ወይ?

በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ብሄራዊ ምርጫ የተጀመረው እንደ ኣውሮፓውያን ኣቆጣጠር በ1957 በዓጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲሆን በ1955 የወጣውን ህገ -መንግስት መሰረት ያደረገ ንጉሱንና የላይኛውን ቤት ወይም ሴነቱን የማይመለከት ነገር ግን የተወካዮች ምክር ቤት ኣባላትን መምረጥ ተጀምሮ ነበር። እማኞች ሲነግሩን ምርጫውና ቆጠራው ግን ሃቀኛ ነበር ኣሉ። ታዲያ ንጉሱ በነበሩበት ዘመን የነበሩት ምርጫዎች ጅማሪያቸው መልካም ቢሆንም ዓለም በማህበራዊ ለውጥ ላይ በነበረችበት በመጨረሻው ሰዓት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ህገ-መንግስታዊ ሞናርኪ ቀይሮ የፖለቲካውን ስልጣንና የህዝቡን ተሳትፎ ማስፋት ስላልተቻለ ወታደራዊ ደርግ ኣብዮቱን ኣንግቦ ብቅ ኣለ።
በዚህ ምክንያት በደርግ ዘመን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ስላልነበረ ምርጫዎች ተካሄዱ ማለት ኣይቻልም።
ዓለም ወደ ዴሞክራሲ በጣም በተዘረጋችበት፣ ብዙ ኣገራት ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በጣም ባደጉበት ጊዜ ወደ ስልጣን የመጣው ወያኔ መራሽ የኢህዓዴግ መንግስት ደግሞ ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ጀምሮ ላለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ኣራት ምርጫዎች የተደረጉ ሲሆን ኣምስተኛው ምርጫ የፊታችን ግንቦት ወር ላይ ይካሄዳል። ያለፉትን ኣራት ምርጫዎች ስናይ ሁሉም ዓለም ኣቀፍ ደረጃቸውን ያልጠበቁ በሚል የተከሰሱ፣ በተለይም የ1997ቱ ምርጫ የህዝብ ቅስም የሰበረ፣ ስብራቱም እስካሁን ያላገገመበት ሁኔታ በስፋት ይታያል።
እነዚህ ኣራት ያለፉ ምርጫዎች ስለምን እክል የበዛባቸውና በጣም የሚታሙ ሆኑ? ከመሰረቱ የምርጫ ችግር ኣለ ማለት ነው? ኣሁን ለኣምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ምርጫስ በምን ይለያል? በኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ከባቢ ኣለ ወይ? ተስፋ እናድርግ ወይ? ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ መሰረታዊ ነገሮች ምን ምን ናቸው? በነዚህ መስፈርቶች ሲመዘን በውኑ ምርጫ በኢትዮጵያ ኣለ ለመባል ያስችላል ወይ? የሚሉትን የመወያያ ኣሳቦች ኣውራጅ ኣድርገን ጥቂት ብንወያይ ደስ ይለኛል።
በውኑ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ይታሰባል ወይ? ብለን ኣጥብቀን ስንወያይ በመጀመሪያ ምርጫን ለማካሄድ ምን ምን መሰረታዊ ጉዳዮች መሟላት ኣለባቸው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ኣንድ ሁለት ተብሎ በግልጽ መቀመጥ ኣለበት ብየ ኣመንኩ። ከዚያም ከነዚያ መስፈርቶች ኣንጻር የኢትዮጵያን ሁኔታ መገምገሙ ችግሩን በግልጽ ያሳያል ከሚል እምነት ነው። በዚህ መሰረት ዋና ዋና የምርጫ ምሰሶና ማገር ያልኳቸውን 8 ጉዳዮች እነሆ
ለኣገርኣቀፍምርጫብቁየሚያደርጉጉዳዮች
1. እምነት
2. ዋስትና
3.ብሄራዊ ማንነት
4. ታዛቢ
5. የተቋማት ነጻነት
6. ኮንስትቲየንሲ
7. የፖለቲካ ለሂቁና ፓርቲዎች
8. ካምፔን
እንግዲህ ከፍ ሲል ባነሳናቸው ነጥቦች ኣንጻር ሲታይ በኣሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የለም ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል። ችግሮቹ መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን በኣጠቃላይ መሰረታዊ የሆኑ የምርጫ መጫወቻዎች ፈጽመው የሉም። የሚያሳዝን ድምዳሜ ቢሆንም ምርጫ በኢትዮጵያ የለም። ዜጎችም ከምርጫ ሳጥን ለውጥን እናመጣለን ብለው በየኣምስት ኣመቱ መድከም ዋጋ የለውም።
መንግስት የምርጫን ፕሮፓጋንዳ ኣንድ የፖለቲካ የስልጣን ማራዘሚያ መሳሪያ ኣድርጎ ነው የሚያየው። ይህ መታወቅ ኣለበት። በተለይም የዓለም ባንክን፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅትንና የዓለምን ዴሞክራቲክ ኮምዩኒቲ ለመደለል ምርጫ መሳሪያ መሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል።
በኣጠቃላይ ይህ መንግስት በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ከስልጣን የሚወርድበት እድል ወደ ዜሮ የተጠጋ ሲሆን ምን ኣልባት ጥቂት ጭላንጭል የምትታየው ኣንድ ነገር ከተፈጠረ ነው። ምን ኣልባት የታጠቁ ሃይሎች ትግላቸው በርግጥ ከንድፈ ሃሳብነት ኣልፎ ማጥቃት ከጀመሩና ጫና ከፈጠሩ፣ ህዝባዊ እምቢተኝነት በየቦታው ከታየ፣ የፖለቲካ መሪዎች ትግሎችን በየፊናው የመምራት ቁርጠኝነት ካሳዩ፣ የለሂቁ ክፍፍል መጥበብ ካሳየ፣ በቅርቡ ታላቋ ብሪታኒያ እንደወሰደችው ኣቋም ሌሎች ኣገራት ከቀጠሉ፣ መንግስት ምርጫን ሰበብ ኣድርጎ ሸርተት ሊል ይችላል። እነዚህ ኣስገዳጅ ሁኔታዎች ካልገፉ መጪው ምርጫ ተስፋ የሚጣልበት ኣይሆንም።በቅርቡ ታላቋ ብሪታኒያ የወሰደችው ርምጃ በርግጥ የኢትዮጵያውያንን ትግል በጅጉ የሚያግዝ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን በውሳኔው ፈንድቀዋል። ኢሃዴግም ከብሪታኒያ የሚያገኘው 98 ቢሊዮን ብር ነጥፎበታል። ከሌሎች የምእራብ ኣገሮችና ከኣሜሪካ ግፊቱ ከጠነከረ፣ የሰባዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በየፊናው ከከሰሱ ጫናው ስለሚጠነክር ለኢሓዴግ የሚሻለው ኣወዳደቅ በምርጫ ስም ይሻላልና ምን ኣልባት በዚህ መንገድ ምርጫ ተስፋ ሊኖረው ይችላል።ሰላማዊ ታጋዩች በምርጫ የማያምን መንግስትን ይዘው ወደ ምርጫ የሚገቡት የህዝቡን ጉልበት ተማምነው ይመስለኛል። መንግስት እንደፈለገው ምርጫውን ኣጭበርብሮ የሰጣቸውን ጥቂት ወንበር ተቀብለው “ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል” እንደሚባለው ዝም ካሉ ይህ ሰላማዊ ትግል ኣይባልም። ሰላማዊ ትግል ማለት ወደ ምርጫ ሄዶ ምርጫው ሲዘረፍ ዝም ማለት ኣይደለም። ይሄማ የሌባ ተባባሪነት ነው። ስለዚህ መንግስት ሲያጭበረብር ህዝብን በጽናት ማታገል ከሰላማዊ ታጋዮች ይጠበቃል።
በዚህ ኣሁን ባለው የፖለቲካ ኣሰላለፍ ኢትዮጵያ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ ኣትችልም። በተለይ በገዢው ኣካባቢ ትንሽ የሃላፊነት ስሜት ቢኖር ቅድመ ውይይቶች፣ ሰነዶች፣ ዋስትናዎችና ሲስተም ሊዘረጋ ይቻል ነበር። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ስምምነቶች ካልተደረጉ የምርጫ ነገር በኢትዮጵያ የሚታሰብ ኣይሆንም።

No comments:

Post a Comment